The victory of adawa የአድዋ ድል ታሪክ
ምኒሊክ ተወልዶ ባያነሣ ጋሻ
ግብሩ እንቀላል ነበር ይሄን ጊዜ አበሻ፤
***
ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ
መድፍ አገላባጭ ብቻለብቻ፤
***
የአድዋ ሥላሴን ጠላት አረከሰው
ገበየሁ በሞቴ ግባና ቀድሰው፤
የአድዋ ድል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ክብር ማኅተም፤ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተጋድሎ ቀንዲል ነው፡፡
የመላው ዓለም ተፈጥሮአዊ ግብር እና ሰብአዊ ክብር የታደሠው፤ በእውነትና በፍትህ ህልውናና ምልዓት ላይ የተሰካ ትልቅ ጥርስ የተነቀለው
… በአድዋ የታላቅ ህዝቦች ታላቅ ድል ነው፡፡
ከአዲስ አበባ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ስንሄድ 1066 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ታላቁ ጦርነት የተደረገበትና
ታላቁ ድል የተገኘበት ሥፍራ አድዋ ከተማና የከተማው ግድም ገመገሞች ይገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያውያን አቡሻኽር (Julian
calendar) የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም፤ ወይም በአውሮጳውያን የዘመን አቆጣጠር (Gregorian Calendar)
February (የካቲት) መጨረሻ እና March (መጋቢት) መጀመሪያ ላይ 1896. ለጦርነቱ መነሻ የሆነው ውል የተፈፀመው በዚሁ
ዘመን ከአዲስ አበባ በስተሰሜን 468 ኪሎ ሜትር ርቀት ግድም ከውጫሌ ከተማ ግርጌ ከአምባሰል ተራራ ሥር ወሎ ውስጥ ንጉሥ ይስማ
እየተባለ በሚጠራ ሥፍራ ነው፡፡
ሸልዶ ተራራ ወይም (ሶሎዳ ተራራ)፤ ማርያም ሸዊቶ፤ አዲ ተቡን፤ ረቢ አርእየኒ (እግዚሃር አሳየኝ)…
በመሠኘት የሚታወቁት እነዚህ ገመገሞችና ተራራማ ሥፍራዎች ዋነኞቹ የጦር ግንባሮች ናቸው፡፡ በመቶ ሺህ የሚሠላ የኢትዮጵያ ገበሬ
ሠራዊት ከአንድ ቀን ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ የአውሮጳ ቅኝ ገዢ ወራሪዎችን ድባቅ ከመታና ረግጦ ካስወጣ በኋላ ከምሽቱ አራት ሰዓት
ግድም (የካቲት 23 ቀን) እንዳማርያም ላይ ተሰባስቦ በአንድ እግሩ ቆሞ ቀኙን (ድሉን) ለሰጠው አምላክ ምሥጋና አቅርቧል፡፡ አባት
ሆይ፤ ንቀውን የመጡ የአገራችንን ድንበርና ልዕልና የደፈሩ የአውሮጳ ኮሎኒያሊስት ወራሪዎችን እንድናሸንፍ (ድል እንድናደርግ) ስለረዳኸን
እናመሰግንሃለን ...
ሃያ ዘጠኝ ሺህ ፈረሰኞችን ጨምሮ ከመቶ ሺህ እስከ መቶ ሃያ ሺህ የሚገመት አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር
በባዶ እግሩ የተጓዘ የኢትዮጵያ የገበሬ ሠራዊት በወታደራዊ አካዳሚ የሠለጠነውን የአውሮጳ ወራሪ ጦር የካቲት 23 ማለዳ አሥራ አንድ
ሰዓት ግድም ገጥሞ ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ ማሸነፉን አረጋግጧል ይለናል የታሪክ ተመራማሪው ጆርጅ በርክሌይ የአድዋ ጦርነትና ዳግማዊ
አፄ ምኒሊክ በተሰኘና ዳኘው ኃይለሥላሴ ወደ አማርኛ በተረጐሙት መጽሐፉ ላይ፡፡ የኢትዮጵያ ገበሬ ሠራዊት ፈረሱ ላይ ሆኖ የጋሻውን
እምብርት መሬት ላይ እያጠቀሰ ጐራዴውን አየር ውስጥ እየቀዘፈ ባበደ መንፈስ (በተቆጣና በቆረጠ መንፈሥ) በጀግንነት ተዋግቷል፡፡
ጦርነቱ በተጀመረ ከአምስት ሰዓት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ሃምሣ ስድስቱም የኢጣሊያ መድፎች ሙሉ ለሙሉ
ተማርከዋል፤ የቅኝ ገዢውን ወራሪ ሠራዊት ከመሩት ጀኔራሎች ጄኔራል አልቤርቶኒ ሲማረክ የሠራዊቱ ዋና አዛዥ ጄኔራል ባራቴሪ ከጥቂት
አጃቢዎቹና በሽንፈት ከተበታተኑ የኢጣሊያ ወታደሮች ጋር ሸሽቷል፡፡
በዚህ ድብልቅልቅ ያለ ውጊያ ከሃምሣ ስድስቱ የኢጣሊያ መድፎች በተጨማሪ ብዙ ሺህ ቀላልና ከባድ መትረየሶች
እንዲሁም የነፍስ ወከፍ ጠመንጃዎች በአሥር ሺሆችና በመቶ ሺዎች ከሚቆጠሩ መሰል ጥይቶቻቸው ጋር ተማርከዋል፡፡ በአጠቃላይ ምርኮው
ወደ አዲስ አበባ የተጓጓዘው በአምስት መቶ አጋሰሶች ተጭኖ ነው፡፡
በማግስቱ የካቲት 24 ቀን 1888 ዓ.ም ከጠዋቱ አራት ሰዓት ላይ የኢጣሊያ ምርኮኞች በምኒሊክ ድንኳን
ፊት ሲያልፉ የኢትዮጵያ ጀግና የገበሬ ሠራዊት እየፎከረ እየሸለለ አሳልፉዋቸዋል፡፡ ጄኔራል አልቤርቶኒ በምርኮኛነት ኢትዮጵያ ውስጥ
ቆይቶ አገሩ ከተመለሰ በኋላ በፃፈው መጽሐፍ ላይ ከሚፎክሩት ጥቁር የነፃነት ተዋጊዎች መሃከል አንዱ እንደ እኛው ነጭ አውሮጳዊ
ነው ብሎአል፡፡ ይህ ሰው ከፈረንሣይ አገር ወደ ኢትዮጵያ ለጦር መሣሪያ ጥገና የመጣ ካፒቴን ኦርዲናንስ ሲሆን፤ አሁን ጊዜው የጦርነት
ስለሆነ ወደ አገርህ ተመለስ ቢባል ቢሠራ አሻፈረኝ ብሎ ከእኛ ጋር አድዋ ድረስ የዘመተ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በአድዋ ጦርነት ላይ ከተዋጋችባቸው የጦር መሣሪያዎች ሠማንያ ሺህ የሚሆኑት አሮጌ ጠመንጃዎች
የተገዙት ከፈረንሳይ አገር በምሥጢር ነው፡፡ ጠመንጃዎቹን ገዝተው ወደ ኢትዮጵያ ያስገቡት ለመጀመሪያ ጊዜ መኪና ወደ ኢትዮጵያ ያስገቡት
በሥጋ በደምና በትውልድ አርመናዊ በነፍስና በመንፈስ በዜግነትና በልብ ፍቅር ኢትዮጵያዊ የሆኑት የኢትዮጵያ የልብ ወዳጅ ሰርኪስ
ቴሪዝያን ናቸው፡፡
አሁን በመዲናችን የሚገኘው የአርሾ ላቦራቶሪ ባለቤትና በዓለም ላይ ኢትዮጵያን የመሰለ ውብ አገር
የለም ያሉኝ ዶክተር አርሻቪር ቴሪዝያን ኢትዮጵያ ውስጥ አርመናዊ ትውልድ ኖሮት ኢትዮጵያዊ ዜግነት የሌለው (ኢትዮጵያዊ ያልሆነ)
አርመን ያለመኖሩን ያጫወቱኝ ከአሥራ አምስት ዓመታት በፊት ነው፡፡ የሠማንያ ሺህ ጠመንጃዎቹን አገዛዝ ሁናቴ የሚያውቁት ደግሞ ከአርሾ
ቀደም የሚሉትና ከአሥራ ስድስት ዓመታት በፊት ለሪፖርተር ጋዜጣ ይሄንኑ በአንደበታቸው የገለፁት አቬዲስ ቴሪዝያን ናቸው፡፡ ሠርኪስ
ቴሪዝያን ጠመንጃዎቹን ከገዙ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ያስገቡት በጅቡቲ በኩል ነፋስ ባህሩን ሲያነሳና እንደ ግድግዳ ሲያቆም በዚያ ተፈጥሮአዊ
ክንውን በመጠቀም ደብቀውና ሸሽገው ነው፡፡
የአድዋ ድል ለመጀመሪያ ጊዜ የተከበረው በሠባተኛ ዓመቱ በ1895 ዓ.ም (እ.ኤ.አ በ1903) ከአንድ
መቶ ዘጠኝ ዓመታት በፊት አሁን ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ያለበት ሥፍራ ምኒሊክ አደባባይ ነው፡፡ በክብረ በዓሉ (በድል በዓሉ) ላይ
ዲፕሎማቶችና የውጪ አገር መንግሥታት ተወካዮች አርበኞች የመንግስት ባለሥልጣኖች ብዙ ሺህ ፈረሰኞችና ሥፍር ቁጥር (ወፈ ሠማይ የሆኑ)
ኢትዮጵያውያን ከሊቅ እስከ ደቂቅ መገኘታቸውን፤ ከፈረሰኞቹ ብዛት የተነሳ ፀሐይ በአቧራ እስከመጋረድ መድረሷን ጳውሎስ ኞኞ የኢጣሊያና
የኢትዮጵያ ጦርነት በተሰኘ መጽሐፉ ላይ ጽፎአል፡፡ እንዲሁም ተክለፃዲቅ መኩሪያን የመሳሰሉ ኢትዮጵያውያን የታሪክ ተመራማሪዎችና
የውጪ አገር ዜግነት ያላቸው ፀሐፍትና ተመራማሪዎች በተለያዩ መፃሕፍቶቻቸው ይሄንን አሣምረው ጽፈውታል፡፡
ታላቁ የጥቁር ህዝቦች ድል (የአድዋ ድል) በመላው ዓለም ፖለቲካ ላይ ከፍተኛና ዋነኛ ለውጦች አምጥቶአል፡፡
የእንግሊዝ ጋዜጦች በአድዋ ድል ማግስት የዓለም ታሪክ ተገለበጠ ታላቅ የትውልድ ኃይል በአፍሪቃ ተቀሰቀሰ … ብለው ፃፉ፡፡ በኢንሳይክሎፒዲያ
ብሪታኒካ፡- ዘመናዊት ኢትዮጵያን የፈጠረ የተባሉት ዳግማዊ ዓፄ ምኒሊክ በሌሉበት (እርሳቸው በአካል ባልተገኙበት የነፃነት ተጋድሎ
መሪዎች ጉባኤ) የአፍሪቃና የመላው ዓለም ጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተጋድሎ መሪ ተደርገው ተመረጡ፡፡
ጦርነቱ ከመደረጉ በፊት እ.ኤ.አ በ1880ዎቹ መጀመሪያ ጀርመን አገር በርሊን ከተማ ላይ በተደረገው
የአውሮጳ ቅኝ ገዢ (ኮሎኒያሊስት) መንግስታት ሥልጣናትና ልሂቃን የጦር ጄኔራሎችና ሊቃውንት ስብሰባ ላይ ጥቁር ትልቅ ትል ነው
ቅንቡርስ ነው እንጂ ነፍስ ያለው ሰው አይደለም ብለው የነበሩ አፈሩ፤ እውነትና ፍትህ ኢትዮጵያና አፍሪቃ ከበሩ፡፡ ከሲግመንድ ፍሮይድ
የሳይኮ አናላይሲስ ጥናትና ምርምር በፊት፡- ጥቁር ህዝብ ትልቅ ትል ላይሆን ነፍስ ያለው ሰው ከሰውም ሰው ጀግና መሆኑን በተጨባጭ
ያስመሰከረ የኢትዮጵያ ገበሬ ሠራዊት ነው፡፡
ከፈረንጅ የአውሮጳ መንግሥታት ሩሲያና ፈረንሳይ የአድዋን ድል ከልብ ደገፉ፡፡ ጀኔራል ባራቴሪ በአገሩ
በኢጣሊያ ጦር ፍርድ ቤት ቀርቦ ማዕረጉ ተገፈፈ፡፡ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲኞር ክሪስፒ በፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን ለቀቁ፡፡
የኢጣሊያዊው ንጉሥ አማኑኤል ኡምቤርቶ የልደት ቀን የሀዘን ቀን እንዲሆን ተወሰነ፡፡ ሮማ (ሮም)ን
ፍሎሬንስን ሚላኖ (ሚላን)ን ቬነስን…የመሳሰሉ የኢጣሊያ ከተሞች ምኒሊክ ለዘላለም ይኑር በሚሉ የተቆጡ አውሮጳውያን ትዕይንተ ህዝብ
አድራጊዎች ተጥለቀለቁ፡፡ ኢትዮጵያ በአድዋ ጦርነት ወቅት በዋናው የጦር ግንባር ገጥማ በፍልሚያ ድል ማድረግ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ
በአራት መስክ ሠለጠነች በምትባለው አውሮጳዊት አገር ኢጣሊያ ላይ ድል ተቀዳጅታለች፡፡ ይኸውም፡- በጦርነት እና በወታደራዊ መረጃ
(Military Security intellegence)፤ በዲፕሎማሲና በፖለቲካ ጥበብ ነው፡፡
በፖለቲካ ጥበብ በኢጣሊያ ቅኝ ገዢ ብልጣብልጥ የመንግሥት ሥልጣን ላይ ድል የተቀዳጀችው ገና ጦርነቱ
ሳይጀመር ለጦርነቱ መጀመር መነሻ የሆነው የውጫሌ ውል በተደረገበት ሥፍራ ነው፡፡
የውጫሌ ውል አንቀጽ አሥራ ሰባት የጣሊያንኛው፡- ኢትዮጵያ ከአውሮጳ መንግሥታት ጋር ማድረግ የምትፈልገውን
ግንኙነት በኢጣሊያ መንግስት በኩል ማድረግ አለባት ሲል፤ አማርኛው ደግሞ ኢትዮጵያ ከአውሮጳ መንግሥታት ጋር ማድረግ የምትፈልገውን
ግንኙነት በኢጣሊያ መንግሥት በኩል ማድረግ ትችላለች ይላል፡፡
የአማርኛው የኢትዮጵያን ሉአላዊነትና ልዕልና ያከብራል፤ የጣሊያንኛው የኢትዮጵያን ሉአላዊነትና ልዕልና
መድፈር ብቻ ሳይሆን ብሔራዊ ክብሯንና ጥቅሟን ይነካል፡፡ ይሄን የተገነዘቡት የኢትዮጵያ መሪዎች የውሉ አንቀጽ አሥራ ሰባት የጣሊያንኛ
ትርጓሜ የኢትዮጵያን ክብርና ጥቅም በማይነካና ሉአላዊነቷን በሚያከብር መልኩ እንዲስተካከል በተደጋጋሚ ወተወቱ፡፡ መወትወቱ ውጤት
ሳያመጣ ቢቀር፤ ምኒሊክ፡- መዘግየት አደገኛ ነው ጣይቱ አሉ፤ ስለዚህ ጉዞ ወደ ወሳኙ ጦርነት (ማድረግ) የግድ ነበር፡፡
የኢትዮጵያን አገራዊ ክብርና ጥቅም ህልውናና ልዕልና ሲሆን ሲሆን በውድ ካልሆነ ደግሞ ሳይወድ በግድ
ማስከበርና ማስጠበቅ የአንድ አገር መንግሥት ዋነኛ ግዴታና ኃላፊነት ነው፡፡
ስለዚህ አባቶቻችን (የጥንት ወላጆቻችን) ውትወታቸው አልሰማ ቢል ጦር እንግጠም አሉ፡፡
ይሄ የፖለቲካ ጥበብ ብልጫ ወይም ድል ነው፡፡
በወታደራዊ መረጃ (Military Security intellegence) ብልጫ የኢንቲጮ ተወላጅ በሆኑት
ባሻዬ አውአሎም ሀረጐት አማካይነት ኢትዮጵያ ሠለጠነ የተባለውን የአውሮጳ ኃይል አሸንፋ ጣሊያኖች ባልፈለጉት ቦታና ባልመረጡት ጊዜ
ወደ ጦርነት እንዲገቡ አድርጋለች፡፡
በወታደራዊ ሣይንስ (Military Science) አገባብ ለጦርነት የተንቀሳቀሰ አንድ ሠራዊት ወዲያውኑ
ወደ ጦር ግንባር መግባት አለበት፡- ይሄ አንድ ነጥብ ነው፡፡ ሌላው ነጥብ አንድ ለግዳጅ የተንቀሣቀሠ ሠራዊት ለመሰናዶም ሆነ ለመከላከል
ውጊያ በአንድ የመከላከያ ወረዳ ከሠፈረ በዚያ መከላከያ ወረዳ ከስድስት ወራት በላይ መቆየት የለበትም፡፡ በአንድ ቦታ ላይ ከስድስት
ወራት በላይ ከቆየ ሊደርስ የሚችል የወታደራዊ ሥነልቦና (Military Psychology) ጉዳት አለ፡፡ የመሸገበትን የመከላከያ
ወረዳ እየተለመማመደ ሲሄድ ስለሚዘናጋና የውጊያ ስሜቱ እየቀነሰ (እየቀዘቀዘ) ስለሚመጣ ጉዳት አለው፡፡ ከሎጂስቲክ አኳያ የውጊያ
ዝግጁነቱም አደጋ ላይ ስለሚወድቅ (በሌላ አነጋገር ስንቅ እየጨረሰ ስለሚሄድ) በነዚህ ምክንያቶች በአፋጣኝ ወደ ጦርነት መግባት
ለሠራዊቱ ድል አድራጊነት ትልቅ ጥቅም አለው፡፡
የኢትዮጵያ በሠላም ጊዜ ገበሬ በጦርነት ጊዜ ጀግና ተዋጊ እንጂ ዘመናዊ ወታደራዊ መሠረት ያለው Professional Army ባልነበራት በዚያ ዘመን ለአንድ መቶ ሃያ ሺህ
ሠራዊት የሎጂስቲክ አገልግሎት እየሰጡ ለረጅም ጊዜ መቆየት አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለዚህ የጀግንነት ግለት ሳይበርድ የሎጂስቲክ (ስንቅ
ትጥቅ መድሃኒት) አቅም ሳይዳከም በፍጥነት ጦር መግጠም እጅግ አስፈላጊ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ሠራዊት ጦርነቱን ፈጥኖ ለመግጠም ጣሊያኖች
ወደ አድዋ መምጣት አለባቸው፤ ወይም ደግሞ የእኛ ሠራዊት ጣሊያኖች ወደመሸጉበት የኤርትራ ከፍተኛ ቦታዎች መሄድ አለበት፡፡ ከነዚህ
ሁለት ሁኔታዎች የአንደኛው መሆን የግድ ነበር፡፡ ወደ ጣሊያኖች መሄድ ከፖለቲካ ሁኔታዎች ባሻገር ከወታደራዊ ሳይንስ አንፃር የሚመረጥ
አይደለም፡፡ በምሽግ ውስጥ ሆኖ የሚከላከል ሠራዊትና ከምሽግ ወጥቶ የሚያጠቃ ሠራዊት መስዋዕትነት የመክፈል ዕድሉ እኩል አይደለም፤
ለሚከላከል አንድ ወታደር ሶስት የሚያጠቃ ወታደር ነው የሚያስፈልገው፡፡
ስለዚህ ጣሊያኖች ወደ አድዋ እንዲመጡ ማድረግ የግድ ሆነና የአድዋ ድል ቁልፍ የምላቸው የአርባ ዓመቱ
ጐልማሣ ባሻዬ አውአሎም ሀረጐት ተጠሩና ለአንድ ታላቅ አገራዊ ኃላፊነት እንዲሠናዱ ተደረገ፡፡ ይሄ ሁሉ በምሥጢር ነው የተከወነው፡፡
በሚቀጥሉት ቀናት አውአሎም ለኢጣሊያ ኮሎኒያሊስት ወራሪዎች ከሚሠልሉ የአገር ተወላጆች (ፌርማቶሪዎች) ጋር ወደ ባራቴሪ ተላኩ፡፡
ከመሄዳቸው በፊት ስንቅ ማለቁና ተስቦ በሽታ በሠራዊቱ ውስጥ መግባቱ ፌርማቶሪዎች ባሉበት ተለፈፈ፡፡ አውአሎምና ፌርማቶሪዎቹ ወደ
ኤርትራ ዘልቀው ለጄነራል ባራቴሪ ይሄንኑ ነገሩት፡፡
ባራቴሪ ጊዜው አሁን ነው አለና የካቲት 22 አመሻሽ ላይ በአውአሎም መሪነት ሠራዊቱን ይዞ ወደ አድዋ
ተመመ፡፡ የካቲት 21 እንዳይነሣ ዝናብ ስለያዘው እንጂ ታላቁ ጦርነት የካቲት 22 ሊደረግ ይችል ነበር፡፡ ስለዚህ ጄነራል ባራቴሪ
በዝናብ በመያዙ ምክንያት ዘመቻውን በማግሥቱ አደረገና የካቲት 22 ቀን 1888 ዓ.ም ሌሊቱን ሙሉ ሲጓዝ አድሮ ሊነጋ ሲል የካቲት
23 ቀን 1888 ዓ.ም አድዋ ጦር ግንባር ደረሠ፡፡ አውአሎም ከፊት ለፊታቸው የጀግናው የቱርክ ፓሻ የአፍሪቃ ጀኔራል አሉላ አባነጋ
የገበሬ ሠራዊት ምሽግ እንደታያቸው መሮጥ ጀመሩ፡፡ ባራቴሪ፡- አውአሎም አውአሎም ብሎ ተጣራ፡፡ እስሀ ዝዋአልካዮ አያውለና ብለውት
ዘለው አሉላ ምሽግ ውስጥ ገቡ፡፡ ዛሬ አንተን አያድርገኝ ማለታቸው ነው በአማርኛ፡- እስሀ ዝዋአልካዮ አያውለና፡፡
ከጥቂት ደቂቆች በኋላ ምድር ቁና የሆነችበት ድብልቅልቅ ያለው ጦርነት ተጀመረ፡፡ የኢትዮጵያ ጀግና
የገበሬ ሠራዊት ከጠዋቱ አራት ሠዓት ግድም ታላቁን የአድዋ ድል መቀዳጀቱን አረጋገጠ ፡፡ ብዙ ሺህ የኢጣሊያ ወታደሮች በጦር ሜዳ
ተገደሉ፡፡ ብዙ ሺዎች ደግሞ ቁስለኛና ምርኮ ሆኑ፡፡ የተቀረውንና ድል ተመትቶ የተበታተነውን የኢጣሊያ ወታደር እያሣደደና እያባረረ
አፍሪቃዊው ኃይል ፈጀው ብሎ ፅፎአል ጆርጅ በርክሌይ፡፡ ከሚሸሹት መሃከል አንዱ የአውሮጳዊው ወራሪ ሠራዊት ዋና አዛዥ ጄኔራል ባራቴሪ
ነው፡፡
ይሄ (በአውአሎም ብስለትና ሥልጡንነት መስዋዕትነትና ኢትዮጵያዊ ፍቅር የተገኘው) ሰለጠነ በሚባለው
የአውሮጳ ኃይል ላይ አልሰለጠነም በሚባለው አፍሪቃዊ ኃይል የተጨበጠ ትልቅ የወታደራዊ መረጃ (Military Security
intelligence) ብልጫ ወይም ድል ነው፡፡
በወታደራዊ ሣይንስ ደግሞ ወታደራዊ መረጃ ለወታደራዊ ግጃጅ አፈፃፀም ዋነኛና ወሣኝ ጠቀሜታ አለው፡፡
በዚህች ዓለም ላይ ከተደረጉ አብዛኞቹ ጦርነቶች ድል ያደረጉት የወታደራዊ መረጃ ብልጫ የነበራቸውና ፍትህና እውነትን ፖለቲካዊ መሠረት
ያደረጉት ናቸው፡፡ እኛ ሁለቱንም ነበረን፤ ዓላማችን የአገራችንን ጥቅምና ክብር ህልውናና ልዕልና ማስከበር ነፃነታችንን ማስጠበቅ
ሲሆን፡- ይህም የፍትህና የእውነት ነፍሥ ነው፡፡ በአገር ወዳዱ ባሻዬ አውአሎም ሀረጐት አማካይነት ደግሞ በአውሮጳ ላይ የወታደራዊ
መረጃ ብልጫን ተቀዳጀን፡፡ ኢትዮጵያ በረጅም ዘመን ታሪኳ ከውጪ ወራሪዎች ጋር ባደረገቻቸው ጦርነቶች ሁሉ፡- እውነትና ፍትህን መሠረት
አድርጋለች፡፡
የዲፕሎማሲያዊ ድሉን የተቀዳጀችው ኢትዮጵያ፡- አውሮጳ ውስጥ ባስቀመጠቻቸው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ
ወላጅ አባት ራስ መኮንንና ግራዝማች ዮሴፍ በተሰኙ ዲፕሎማቶቿ አማካይነት ነው፡፡ ጣሊያኖች ኢትዮጵያውያን ያልሰለጠኑ በመሆናቸው
በምርኮኞች ላይ ሠብአዊነት የጐደለው ድርጊት ይፈፅማሉ ብለው ያስወራሉ፡፡ ግራዝማች ዮሴፍ በተለያዩ ቋንቋዎች እየፃፈ ለአውሮጳ ጋዜጦች
ይሄን ያስተባብላሉ፡፡ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ደግሞ ኢትዮጵያ ልክ ዲፕሎማቶቿ እንዳሉት ምርኮኞችን ግብር አብልታ አካላቸዉም ምቾታቸውም
ሳይጓደል ወደ አገራቸው ሰደደች፡፡
በዚህም ዲፕሎማሲያዊ ሥልጣኔዋን ለመላው አውሮጳ እና ለመላው ዓለም በተጨባጭ አሳየች፡፡ ከመቶ ዓመታት
በላይ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላት ብቸኛ አፍሪቃዊት አገር፡- ኢትዮጵያ ነች፡፡ የአብዛኞቹ የአፍሪቃ አገሮች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት
ረጅም ዕድሜ ከስድሣ ዓመት አይዘልም፡፡ ኢትዮጵያ፡- ከኢጣሊያና ከፈረንሣይ ከአሜሪካ (USA) እና ከእንግሊዝ ከሩሢያና ከጀርመን
(ከስድስት አገራት) ጋር ከመቶ ዓመታት ለሚበልጥ ጊዜ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን አዳብራ እና አፅንታ ቆይታለች፡፡
በአድዋ ድል፡-
ዋነኛው ድል በጦር ግንባር ፍልሚያ የተገኘው ድል ነው፤ ታላቁ የአድዋ ድል፡፡
የአድዋ ጦርነት የተደረገው በሁዳዴ ፆም ውስጥ ነው፡፡ ከዚያ በፊት በአፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት
የተደረገው የመቅደላ ጦርነትም በሁዳዴ ፆም ውስጥ ነው የተካሄደው፡፡ በአድዋ ጦርነት ፆምና ውጊያ አብሮ ስለማይሄድ ግብፃዊውን ጳጳስ
ሠራዊቱን ይፍቱትና እንደ ልቡ ይዋጋ ቢባሉም ባለመፍታታቸው ከኢትዮጵያ የገበሬ ሠራዊት ጿሚ የሆነው እየፆመ ለመዋጋት ተገዶአል፡፡
በመቅደላ ውጊያ ዓፄ ቴዎድሮስ [ካሣ ኃይሉ ወልደጊዮርጊስ (አባ ታጠቅ ካሣ) (መዩሣው ካሣ) (ወሬሣው ካሣ)] ሊወጋቸው ለመጣው እንግሊዛዊው ጄኔራል ናፒዬርና ሠራዊቱ ፆምህን ፈትተህ ከእኔ
ጋር ውጊያ ግጠም ብለው አንድ ሺህ በጐች ልከውለታል፡፡
ከአድዋ ጦርነት በፊት ባሉት ጥቂት ወራትና ሣምንታት መቀሌና አምባላጌ ላይ የተደረጉ ጦርነቶች አሉ፡፡
የመቀሌን ከተማ በኢጣሊያዊው ኮሎኔል ጋሊያኖ ከሚመራው አውሮጳዊ ሠራዊት ለማስለቀቅ መስዋዕትነቱ የበዛ በመሆኑ፡- መቀሌ የተለቀቀችው
በፈረንጆች ሚሊኒየም BBC (British Broadcasting Corporation) የሚሊኒየሙ ምርጥ ሠብዕና ብሎ ከአህጉር አፍሪቃ
ባጫቸው ከጐንደር ኦሮሞ ቤተሠብ በሚወለዱት እቴጌ ጣይቱ ብጡል ሥልጡን ወታደራዊ መላ ነው፡፡
ዝርዝሩን እዚህ አላወሣውም እንጂ መቀሌ በጣይቱ ልዩ ወታደራዊ ብቃት መያዝዋን መግለፅ ይጠቅማል፡፡
በኋላ ላይ ኮሎኔል ጋሊያኖ በአድዋ ጦርነት ተማርኮ፡- የምንሊክን ፊት ከማይ ግደሉኝ ብሎአል፡፡ በአምባላጌው ጦርነት ሊቀ መኳስ
አባተ መድፍ ተኩሠው በጣሊያን መድፍ አፍ ውስጥ እስከ መክተት የዘለቀ አነጣጣሪነታቸውን አሣይተዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ሥልጣናት፡-
ማዕከል ወሎ ውጫሌ በነበረበት ሁናቴ፤ ዳግማዊ ዓፄ ምኒሊክ (አባ ዳኘው) ለህዝባቸው የክተት ጥሪ ካደረጉ በኋላ ከዳር እስከ ዳር
የተንቀሣቀሠው የተቆጣ ኢትዮጵያዊ ሠራዊት ሢተም፤ ሲገባኝ ከሠሜን ኢትዮጵያ ከጐንደር ከጐጃም ከወሎና ከትግራይ … የተንቀሳቀሰው
አትንኩኝ ያለ ኢትዮጵያዊ ጀግና ከሚተምመው ሠራዊት የተገናኘው በትውልድ አቅራቢያው ሆኖ ነው፡፡
መጓጓዣ በሌለበት ዘመን የሠሜኑን የኢትዮጵያ ጀግና የገበሬ ሠራዊት ወደ ሰሜን ለማዝመት ሲባል በመሀል
አገር ማሰባሰብ የሚያስፈልግበት ሁኔታ አልነበረም፡፡
ይህመረጃጠቃሚሆኖካገኙትለሌሎችምእንዲደርስshareያድርጉ
Nestamereja.blogspot.com
┈┈┈••●◉❖◉●••┈┈┈
The victory of adawa የአድዋ ድል ታሪክ
Reviewed by nestamereja
on
6:39 AM
Rating:
No comments: