የሳይኮሎጂ ምክሮች - sychology

ሰዎች ስለእኛ በሚያስቡት ነገር ላይ መጨነቅን ለማቆም ቀላል ዘዴዎች
(በአለበል አዲስ)
‘’የማይባል ነገር ተናገርሁ እንዴ? እንዴት እንደዚህ አደርጋለሁ? ሰዎች እኮ መሃይም :ገገማ:የሚያናድድ ሰው ነው/ነች ይሉኝ ይሆናል’’  እያልን ራሳችንን የምናስጨንቅ ስንቶቻችን ነን! ሌሎች ሰዎች ስለእኛ በሚያስቡት ነገር ላይ በመጨነቅ አእምሯችንን በጨለማ ቦታ እንዲንከራተትና ራሳችንን በመጠራጠር የስጋት ስሜት እንዲሰፍንብንና እንዳንረጋጋ እያደረግን መሆኑን ልናውቅ ይገባል:: ለነገሩ ሁላችንም ሰዎች ስለእኛ ያላቸው ሃሳብ/አስተያየት ምን ይሆን ብለን መጨነቅ እንደሌለብን እናውቃለን ወደ ተግባር ለመቀየር  ግን ስንቸገር እንታያለን:: ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ዘዴዎች ብንጠቀምባቸው ይረዱናል!
1. የሰዎችን አዕምሮ ማንበብ እንደማንችል መረዳት፡- እስኪ ሰዎች ስለእኛ የሚያስቡትን በእርግጠኛነት ማወቅ እንችላለን? ብዙ ጊዜ ነገራትን ሳናጣራ ይሆናል በማለት ብቻ ማወቅ እንደምንችል ነው የምናስበው ይህ አስተሳሰባችን ደግሞ ለህይወታችን ፀር ወደሆኑ ድምዳሜዎች/ዉሳኀኔዎች ይመራናል::ስለዚህ እነዛ ሰዎች ሃሳባቸውን የሚገልጹበትን ዕድል አግኝተው ሃሳባቸውን እስካልገለጹልን ድረስ ስለምን እንደሚያስቡ ማወቅ በፍጹም አንችልም፡፡
2. በቋሚነት ለሚጠቅመን ነገር መስራት:- ከሌሎች  ሰዎች የሚሰነዘሩ  የኩነኔ አስተያየቶች በእርግጥም እኛን ይጎዱናል ነገር ግን ከእነዚህ ሰዎች የሚመጣውን አሉታዊ ምላሽ በመፍራት የምናጣቸው/የምናሳልፋቸው መልካም ዕድሎች ጥለውብን ከሚያልፉት የአእምሮ ጠባሳ አይበልጥም፡፡ እነዚህ የኩነኔ/አሉታዊ አስተያየቶች የሚያደርሱብን ጉዳት ቅጽበታዊ ሲሆን ባጣናቸው/ባመለጡን መልካም ዕድሎች ምክንያት የሚደርስብን ጸጸትና ቁጭት ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ ስር እየሰደደና እያደገ ነው የሚሄደው፡፡ ስለዚህ በቋሚነት የሚጠቅመንን ነገር ለማግኘት ጊዜያዊ የሆኑ ተቀባይነት ማጣትን ለመቀበል ፈቃደኞች እንሁን::
3. ራስን ከመኮነን/በራስ ላይ ከመፍረድ መቆጠብ:- እስኪ ሰዎች ምን ይሉን ይሆን ብለን የምንጨነቅበትን ሃሳብ ለሰከንድ ቆም ብለን እናስበው! በእርግጠኝነት እኛ ለራሳችን የምናስበውን ነገር ላይ ነው ሌሎችም እንደዚ ያስባሉ ብለን የምንሰጋ፡፡ ስለዚህ በራሳችን ላይ መፍረድን አቁመን(ራስን ከመኮነን ተቆጥበን) እኛነታችንን ከተቀብለነው ወይም ለራሳችን ጥሩ ግምት ከሰጠን ሌሎቹ ስለእኛ ለሚሰጡት/ለሚያስቡት ሃሳብ ፍርሃትና ስጋት አይኖረንም ማለት ነው፡፡
4. ሌሎች ሰዎችን መኮነንን/በሌሎች ላይ መፍረድን ማቆም፡- ሰዎችን እየገመገምን፡እየኮነንና እየፈረድንባቸው የምንኖር ከሆነ እነሱም በተመሳሳይ ሁኔታ እንደሚፈርዱብን ነው የምናስበው፤ ስለዚህ በእነሱ ላይ ከመፍረድ ይልቅ ህይወታችንን ለማሻሻልና ለማደራጀት እንደሚያግዙን ቆጥረን ብናደንቃቸውና ብናበረታታቸው የበለጠ ተጠቃሚዎች መሆን እንችላለን፡፡
5. ስለእኛ አለመሆኑን መረዳት፡- ሰዎች በራሳቸው እይታ ከደረሰባቸው ክስተት፡ ቁስል፡ ፍራቻና እንከን የተነሳ ለነገሮች የተለያዩ አሉታዊ ምላሾችን ይሰጣሉ ነገር ግን የእነሱ ምላሽ ከእኛ ጋር የሚገናኝ እንዳልሆነ ልብ ልንል ይገባናል፡፡ ለምሳሌ የሆነ ቢዝነስ ለመጀመር ብንወስንና አንድ ሰው ”እመነኝ ይህንን ስራ ከጀመርህ በሚቀጥሉት ወራት አሊያም ዓመታት ምንም  ዓይነት የእረፍት ጊዜ አይኖርህም” ቢል ሰውዬው የተናገረው ቢዝነስ መጀመር ላይ ያለውን ሃሳብ/አመለካከት እንጂ እኛን በተመለከተ እንዳልሆነ ለይተን መረዳት ይጠበቅብናል::
6. በሚያስደስተን ነገር ላይ ትኩረት ማድረግ:- ይህን ባደርግ ሰዎች ይፈርዱብኛል በማለት የሚያስደስቱንን ተግባራት ከማድረግ የምንገደብ ከሆነ(የማኅበረሰቡን እሴቶች በጠበቀ መልኩ) ጊዜያችንን ምንም ዓይነት ጥቅም በሌለው ጭንቀት እያባከንነው መሆኑን እናስተውል፡፡ ስለዚህ በህይወታችን ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት የሚችለውን ብርቅ የሆነውን አቅምና ኃይላችንን በመሸርሸር ፈንታ እኛን በሚያስደስቱን ነገራት ላይ ትኩረት ልናደርግ ይገባል፡፡
7. የሚያውኩንን ነገሮች መለየት፡– ሌሎች ሰዎች አሉታዊ በሆነ መልኩ ይገመግሙናል/ይፈርዱብናል ብለን የምንጨነቀው ምናችንን በተመለከተ ነው? በስራችን ሁኔታ: ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት: ምናልባትም በክህሎታችንና ነገሮችን በመመርመር ባለን አቅም ሊሆን ይችላል:: ስለዚህ በውስጣችን መረጋጋት እንዳይኖር የሚቀሰቅሱ ነገሮችን መለየትና ማሻሻል ከቻልን ማሻሻል አሊያም እንዳሉ መቀበል ያስፈልጋል:: ምክንያቱም ከሁኔታዎች ጋር ሰላም መፍጠር ከቻልን የሰዎች አጸፋዊ ምላሽ አያስጨንቀንም ማለት ነው::
8. ራሳችንን መቀበል:– ፍጹም አለመሆናችንን፡ እንከንና ድክመቶች እንዳሉን መቀበል ነገር ግን አቻ የሌለን(ልዩ) በዓለም ላይ እኛን የሚመስል ሰብዕናና ተሰጥኦ የታደለ ሰው እንደሌለና ወደፊትም እንደማይኖር ልናስተውል ይገባል፡፡
9. አጸፋዊ ምላሾችን መጠበቅ/ተስፋ ማድረግ፡- በሰዎች ዘንድ የሚፈጠረውን አጸፋዊ መልስ በመፍራት ፈንታ ያ ምላሽ ሊፈጠር እንደሚችል አስቀድመን ተስፋ ማድረግ አለብን(የሰዎችን ስሜት ለመቀስቀስ መፍራት የለብንም) ምክንያቱም በሰዎች ዘንድ አሉታዊም ይሁን አዎንታዊ ምላሽ መፍጠር ካልቻልን ምናልባትም ራሳችንን የመሆን ድፍረቱን ልናጣ እንችላለንና፡፡
10. እየኮነኑን/እየፈረዱብን ነው ብለን ካሰብናቸው ሰዎች ጋር ማውራት፡- እንዲያው ሁኔታዎች ተመቻችተውልን ስለእኛ መጥፎነት ያስባሉ/እየፈረዱብን ነው ብለን ከምናስባቸው ሰዎቸ ጋር ተቀራርበን ብናወራ እስከምንገረም ድረስ ምንም ባለጠበቅነው ሁኔታ አዕምሯቸው በብዙ ጭንቀቶች እንደተሞላ ልናውቅ እንችላለን፡፡ ማን ያውቃል ልክ እኛ እንደምንጨነቀው እነሱም ሌሎች ሰዎች ስለእነሱ ምን ሊያስቡ/ሊሉ በሚችሉት ሃሳብ እየተጨነቁ ሊሆን ይችላል እኮ፡፡ ስለዚህ ራሳችንን ግልጽ በማድረግ ከእነዚህ ሰዎች ጋር ተቀራርበን ሃሳብ ማንሸራሸር ያስፈልጋል::
በአጠቃላይ ከላይ የተዘረዘሩትን ሃሳቦች ወደ ተግባረ ከቀየርናቸው እኛም መቀየር እንችላለን!


ስኬት ምንድን ነው? የስኬት ቁልፍስ? በሳይኮሎጂስቶች እይታ (በነጋሽ አበበ)

ስኬታማ ሕይወት እንዴት ያለ ነው? ሰዎች “ለእኔ ስኬት ማለት ይኼ ነው ይኼ ነው” ብለው ሀሳባቸውን በሚገልፁበት ወቅት ስምም የሆነ አገላለፅ መስማት የተለመደ አይደለም፡፡ ለአንዱ እንደ ስኬት የሚታይ ነገር ለሌላው እዚህ ግባ የማይባል ጉዳይ ሊሆን ይችላል፡፡ ቤተሰብ መስርቶ፣ ልጅ ወልዶ ወዘተ ማሳደግ ለአንድ አንድ ሰዎች ትልቅ የሕይወት ስኬት ነው፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ ለሌሎች ዓለምን እየተዘዋወሩ ማየት የስኬት ሁሉ ስኬት ሊሆን ይችላል፡፡ የትኛው ሕይወት ነው ስኬታማ ሕይወት ከሚለው ጥያቄ ጀምሮ ወደዛ በስኬት አሸብርቋል ወደምንለው ሕይወት የሚወስደን ጎዳናስ የትኛው ነው የሚለው ጥያቄ መሰረታዊ ጥያቄ ነው፤ የታሰበበት እና የተጠና ምላሽም ይፈልጋል፡፡
በስነ ልቡና ባለሙያዎች ዘንድ ከሞላ ጎደል የሚያግባባው አንዱ ሀሳብ “ስኬታማ ሕይወት ሚዛናዊ ሕይወት ነው” የሚል ነው፡፡ ሕይወት ብዙ ፈርጆች፣ ገፆች እና ጎኖች አሏት፡፡ ሁላችንም አነሰም በዛ እዚህ ምድር ላይ በምንኖርበት ወቀት የተለያየ ሚና እንጫወታለን፤ የተለያየ ኃላፊነት እንሸከማለን፡፡ ታዲያ እነዚህ የተለያዩ የሕይወት ግፆችን ሚዛናዊ በሆነ መልኩ በሕይወት ወጣ ገባ መንገድ ላይ መኖር መቻል ስኬትም የስኬት ቁልፍም ነው፡፡ ዝነኛው ሳይኮሎጂስት ሲግመንድ ፍሮይድ “ስራ እና ፍቅር የሰው ልጅ ሕይወት የማዕዘን ራስ  ናቸው (Love and work are the corner stone of our humans)” ይላል፡፡ በአጭሩ እነዚህን ሁለት የሕይወት ገፆች ፍሬያማ በሆነ መልኩ መኖር መቻል ስኬትም የስኬትም ቁልፍ ነው፡፡ አንድ ሰው በስራው እጅግ በጣም ውጤታማ ቢሆንና ለወዳጅ ዘመዶቹ ግን የረባ እንኳን ጊዜ መስጠት ባይችል ይህ ሰው ሕይወትን በሙላት እየኖራት እና እየተሳካለት ነው ማለት ይቸግራል፡፡ በዙሪያችን ከሚገኙ ሰዎች ጋር ፍቅር በፍቅር ሆነን ውጤታማ ስራ መስራት ካልቻልንም ያው ነው፡፡ ስኬት እነዚህን ሁለት የሕይወት ገፆች የሚጠይቁትን ጊዜ መስጠት መቻል፣ ሁለቱም የሚያሸክሙንን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት፣ በሁለቱም በኩል አትራፊ መሆን መቻል ነው፡፡
ሚዛናዊ ስለመሆን ስንነጋገር ከእኛ ውጪ ያሉ የሕይወት ገፆችን ብቻ ሳይሆን እኛ ውስጥ የሚገኙ የማንነታችንን ክፍልፋዮች ሚዛንም ሚዛን መጠበቅ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ አንድ ሰው አንድ ሰው ብቻ አይደለም፡፡ አንድ ሰው ውስጡ በሚገኙት የተለያዩ የማንነት ክፍሎች ምክንያት ብዙ ሰውም ነው ማለት ይቻላል፡፡ እነዚህ የተለያዩ የማንነ ክፍሎች የሚፈልጉትን እና የሚያስፈልጋቸውን ያህል ቦታ ከሰጠናቸው፣ ከሰማናቸው፣ ፍላጎታቸውን ካሟላንላቸው፣ አንዱ ከአንዱ ጋር በስምምነት እንዲኖር መፍቀድ ከቻልን ትልቅ ስኬትም የስኬት ቁልፍም ነው፡፡ በአንፃሩ አንዱን ወደፊት አድርገን አንዱን ወደ ኋላ ከተውን፤ አንዱ ዘወትር እንዳሻው እንዲሆን ፈቅደን አንዱ ላይ በር ከዘጋን፤ የአንዱን ጥሪ አድምጠን ሌላውን ጆሮ ዳባ ልበስ ካልን ውስጣችን (አእምሯችን፣ መንፈሳችን ወዘተ) እነዚህ የማንነታችን ክፍሎች የሚራኮቱበት የጦር አውድማ ይሆናል፡፡ በዚህ ምክንያት ልዩ ልዩ ስነ ልቡናዊ ችግሮችም ይፀነሳሉ፤ ይወለዳሉም፡፡ ኤሪክ በርኔ የተባለ ሳይኮሎጂስት የሰው ልጅ ሰብዕና የሶስት ልዩ ልዩ ማንነቶች ጥምረት/ቅንጅት ውጤት ይላል፡፡ የመጀመሪያው “ወላጅ (Parent)” ነው ይላል፡፡ ይህ ክፍል ሁልጊዜ የሚመዝን፣ የሚቆጣጠር፣ እንከን የለሽ ለመሆን ጥረት የሚያደርገው ጥንቁቁ የሰብዕናችን ክፍል ነው፡፡ የዚህ የሰብዕና ክፍል መሰረት ራስ ወዳድነት፣ ደህንነት (security) እና ለሚደርገው ማናቸውም ነገር በቂ ምክንያት (justification) መስጠት መቻል ነው፡፡ ሌላኛው የሰብዕናችን ክፍል “አዋቂ (Adult)” ይባላል፡፡ ይህ የሰብዕና ክፍል ምክንያታዊ፣ አመዛዛኝ እና ነገሮች ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉበትን መንገድ የሚያወቅ ይሆናሉ ወይስ አይሆኑም የሚለውን ጨምሮ መቀየስ መረዳት የሚችለው ነው፡፡ የሚያደርገውን ማናቸውንም ነገር የሚያደርግበት ምክንያት የውስጥ እርካታ፣ የመማር እና የማወቅ ፅኑ ፍላጎት ነው፡፡ ሶስተኛውና የመጨረሻው የሰብዕናችን ክፍል “ልጅ (Child)” የሚል ስያሜ አለው፡፡ ይህ ክፍል በአንፃሩ የፈጠራ አቅሙ የላቀ፤ ሰፊ ምናብ ያለው፤ ማደግ፣ መበልፀግ፣ መጫወት፣ ማጥፋት ወዘተ ነፍሱ የሆነ ነው፡፡ የሚፈልገውና የሚያደርገው ነገር መሰረቱ ደስታ፣ እርካታና ጥፋት ነው፡፡
እነዚህ ሶስት የሰብዕና ክፍሎች አንዳቸው ያለአንዳቸው እንዳሻቸው እንዲሆኑ ብንፈቅድላቸው በጎም በጎ ያልሆነም ውጤት ያስከትላሉ፡፡ አንዱ የሰብዕና ክፍል ብቻውን ፈላጭ ቆራጭ ሲሆን አሉታዊ ነገሮች ሕይወታችን ውስጥ ይበረክታሉ፤ ደስታ ይርቀናል፤ እረፍት ከአድማስ ባሻገር ያለ ሩቅ ሀገር ይሆንብናል፤ ስኬታማ እንደሆንን አይሰማንም፤ ስኬታማ ለመሆን የምናደርገው ትግልም በግጭት የታጀበ ይሆናል፡፡ የደስታ፣ እረፍት፣ ሰላም ወዘተ በጥቅሉ የስኬት ምንጭ እነዚህን ሶስት የሰብዕናችንን ክፍሎች አቻችሎ፣ አስማምቶ እና ሚዛን ጠብቆ ሕይወትን መምራት መቻል ነው፡፡ አንዱን ጥሎ ሌላውን ብቻ አንጠልጥሎ መኖር ተገቢም ገንቢም አይደለም፡፡ የሰው ልጅ ጥልቅ ተፈጥሮአዊ ፍላጎቱ ማደግ፣ አዎንታዊ ለውጥ ማምጣት እና እምቅ ችሎታውን አውጥቶ መጠቀም መቻል ነው፡፡ ይህንን ፍላጎቱን እያሟላ ለመኖር በእነዚህ ሶስት የሰብዕና ክፍሎች መካከል እርቅ፣ ስምምነት እና ሚዛናዊ ግንኙነት ሊኖር ይገባል፡፡ ቅርብ ጊዜ አንድ ትልቅ ፓርቲ ላፍቶ ሞል የመታደም እድሉ ገጥሞኝ ነበር፡፡ ዙሪያዬ ይገኙ የነበሩ ወጣቶች ጨዋታና ቡረቃ ሌላ ነው፡፡ ይዘፍናሉ፤ ይደንሳሉ፤ የራሳቸውን ግጥምና ዜማ እዛው ጭምር እየፈጠሩ ምን አለፋችሁ በቃ ራሳቸውንም በአካባቢያቸው የሚገኘውንም ታዳሚ ዘና ማድረግ ቻሉ፡፡ ምሽቱ እገፋ፣ ወደ ጉሮሮ የሚንቆረቆረው መጠጥ መጠኑ እየጨመረ ሲሄድ ግን ሁኔታዎች መልካቸውን ቀየሩ፡፡ ቅጥ ያጣ ዳንስና ልፊያ፤ የሌላውን መብት የሚጋፍ ድርጊት መፈፀም ተጀመረ፡፡ ያስደሰቱት ሰው ያዝንባቸው፣ ይታዘባቸው፣ ይናደድባቸው ገባ፡፡ ይህ እንግዲህ ሚዛንን መጠበቅ ያለመቻል ውጤት ነው፡፡
መዝናናት እና መደሰት አስፈላጊና እጅግ ጠቃሚ ነገሮች ነው፡፡ ሁሉም ሰው ማንነት ውስጥ መቦረቅ የሚፈልግ “ልጅ” ማንነት አለ፡፡ ይሁን እንጂ ይሄ ማንነት ሙሉ ለሙሉ ወንበሩን ያለ ኃይ ባይ ሲቆጣጠር ከሚለማው ይልቅ የሚጠፋው ያመዝናል፡፡ ይህ ሁኔታ እንዳይከሰት ታዲያ ሀይ ባዩ፣ ከልካዩ፣ ተቆጪው፣ ቆንጣጩ “ወላጅ” ማንነታችን አብሮን ሊኖር ይገባል፡፡ “ይበቃል፤ እንዴ! ተው አንጂ፣ ሰው እኮ እየረበሽክ ነው፣ ኋላ ችግር ውስጥ እንዳትገባ! ነግሬሀለሁ!” ወዘተ ሊል ይገባል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን አመዛዛኙና አዋቂው ማንነታችንም እንዲሁ ምንጊዜም አብሮን ሊሆን ይገባል፡፡ “እየመሸ ነው ብንሄድ ሳይሻል አይቀርም፤ የጀመርካትን ጨርስና ጓደኞችህን ተሰናበት፤ ስትጨፍር ሌላውን ላለመርገጥ ተጠንቀቅ፤ መጠጡንም ቢሆን ከዚህ በላይ አትውሰድ፣ ረሳኸው እንዴ ነገ እኮ ስራ ገቢ ነህ ባለፈው ዓመት እንዲህ ስትጠጣና ስትጨፍር አድረህ የሆንከው ጉድ ትዝ ይልሀል” ወዘተ እያለ አዛዡን እና አማፂውን ማንነታችንን የሚያግባባ፤ ምክንያታዊ እርምጃ እንድንወስድ የሚያግዘን አዋቂ ማንነታችንን ያለ ልዩነት ሊጠነክር ይገባል፡፡ ሶስቱም የማንነት ክፍሎች ድምፅ ኖሯቸው እንደ ዴሞክራሲያዊ ስርዐት “check and balance” እየተደራረጉ ሲኖር ስኬታማ መሆን ይችላል፤ ተፈጥሮአዊ እምቅ ችሎታን አውጥቶ ለመጠቀም የሚያስችል እድል ይፈጠራል፡፡ አንዱ አንዱን ወርሶ ዙሪያ ገባውን ሲያጥር፤ አንዱ ብቻውን አድራጊ ፈጣሪ ሲሆን ግን ውጤቱ ጥፋት፣ ደስታ አልባ መሆን፣ ለመግባባት መቸገር ወዘተ ነው፡፡ ስለዚህ እንደየሁኔታው ሶስቱንም የሰብዕና ክፍሎች ቦታ ሰጥቶ፣ አግባብቶና አቻችሎ፣ ሚዛን ጠብቆ፤ ጨዋታና ጭፈራ አስፈላጊ የሆነበት ቦታ ተጫውቶና ጨፍሮ፣ ቁም ነገር የሚቀድምበት ቦታም እንዲሁ ቁም ነገረኛ ሆኖ፣ ለነገና ከነገ ወዲያም አስቦ፣ ተጠቦ እና ተጠንቅቆ እንደ ወላጅ፣ አዋቂና ልጅ መኖር ስኬትም ነው የስኬትም ቁልፍ ነው፡፡





ቅናት. . . . መቅናትን ማስቀረት እንችላለን!!! – ቁምላቸው ደርሶ



ቅናት መጠኑ ይለያይ እንጅ በአብዛኛው ሰው ላይ የሚታይ ባህርይ ነው፡፡ እኛ ሰዎች በሁለቱም ማለትም ባለንም በሌለንም ቁሳዊም ሆነ ስነ-ልቡናዊ ጥቅሞች ባላቸው ነገሮች ላይ እንቀናለን፡፡ በሌለን ነገር ላይ የምንቀናው ቅናት (Envy) ሰዎች የሚፈልግቱንና እኛ የሌለንን ሲያገኙ ፣ ሲያሳኩ ወይም የሚያሳኩበትን የተስተካከለ መስመር ሲይዙ የሚሰማን ምቾት የማጣት ስሜት ሲሆን፤ ባለን ነገር ላይ ቅናት (Jealousy) ማለት ደግሞ ሌሎች እኛ ያለንን ቁሳዊ አካል ወይም የስሜት ግኙነት የመሰረትንበትን ሰው ሊያሳጧችሁ የሚመስል መጥፎ ስሜት በውስጣችሁ ሲፈጠር ነው፡፡ በምሳሌ ለማስቀመጥም የፍቅር አጋርህን ሌላ ወንድ ሲያናግራት ብታይ እና ሰላም የማጣት ስሜት ሲሰማህ ቅናት (Jealousy) ሸነቆጠህ ማለት ነው፡፡ አልያም ህፃናት አዲስ በተወለደው ወንድም ወይም እህት ምክንያት የሚሰማቸው እናቴን ወይም አባቴን ተነጠኩኝ ዓይነት ስሜት እና ባህርይ እንደ አብነት ማየት ይቻላል፡፡ ቅናት ገደቡን ካለፈ በእኛም ላይ ሆነ በሌሎች ሰዎች ላይ ስነ ልቡናዊ እና አካዊ ጉዳቶችን ይፈጥራሉ፡፡ ሆኖም ግን ቅናትን በበጎ መልኩ የምንጠቀምበት ከሆነ መልካም የሆነ ግንኙነትና እኛ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን በመሙላት ወደተሸለ ደረጃ ወይም የምንቀናባቸው ሰዎች ወዳሉበት የስኬት ማማ ላይ ለመድረስ መንገዱን ይጠርግልናል፡፡
ከላይ እንደተገለጸው ቅናት የተለያዩ ስነ-ልቡናዊ እና አካላዊ ጉዳቶችን ያስከትላል፡፡ ቅናት ቤተሰብን ይበትናል፣ ፍቅረኞችን ያለያያል፣ የስራ ባልደረቦችን ያጋጫል፣ ሰላማዊውን የሰው ልጆች መስተጋብር ያፋልሳል …ባስም ሲል ቅናት ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ህይወትን ያስጠፋል (የዴዝዴሞና ታሪክ ትዝ አላችሁ?) ስለዚህ መፍትሔው ምንድን ነው ?? መቅናትን እንዴት ማቆም እንችላለን??? እስኪ እነዚህን የመፍትሔ አቅጣጫዎች አብረን እንዝለቃቸው………. በጾታዊ ፍቅር ምክንያት ከሆነ ቅናት የሚይዘን በግልጽ መነጋገር፡፡ ይሄ ደርጊትሽ(ህ) ጥሩ ያልሆነ ስሜት እየፈጠረብኝ ስለሆነ መስተካከል ይኖርበታል ማለት አለብን፡፡ ማስተዋል ያለብን ቀንቻለው ማለት የተሸናፊነት ምልክት ሳይሆን ግንኙነቱን ዘላቂና ሰላማዊ ማድረግ እፈልጋለሁ ማለት እደሆነ ነው፡፡( መተማመን) በፍቅር ግንኙነት ውስጥ ዋናው የግንኙነት መሰረቱ መተማመን ነው፡፡ የማይተማመን ባልንጀራ ካብ ለካብ ይማማላል እንዲሉ አበው፤ መተማመን የሌለው  ጾታዊ ፍቅርም ለቅናት የተጋለጠ ነው፡፡ ሌላው መቼም የምንቀናበት ሰው ፍጹም አይደለም፡፡ እሱ የሌለው እኛ ግን ያለን ሌሎች ነገሮችም እንዳሉ መገንዘብ፡፡ሁልጊዜ ራስህን በጥረት ውስጥ ማሳለፍ ይኖርብሃል፡፡ ምክንያቱም የቻልከውን ያህል ስለታተርክ በቅናት ፋንታ እርካታን ታገኝበታለህ፡፡ ከምንቀናባቸው ሰዎች ልምድ መቅሰም አለብን፡፡  ይህም ማለት የቀናህበትን ነጥብ ነቅሰህ አውጣ በዚህም አንተ ማግኘት ያቃተህ ሌሎች ግን ያሳኩት ከሆነ እንዴት እንዳሳኩት በማወቅ ራስህን እንድታሻሽል ይረዳሀል፡፡ በመጨረሻም ሌሎች ሰዎች ላይ እና ያላቸው ነገሮች ላይ ያለህን ፅንፍ የያዘ ትኩረትህን ቀንስ፡፡ ምክንያቱም የአዕምሮህን የትኩረት አቅጣጫ በማስቀየር አቅምህን ያሟጥብሀል፡፡ ስለሌለህ ሳይሆን ስላለህ ነገር በማሰብ ለእራስህ እውቅና ስጥ በዚህም በጊዜ ሂደት በራስ መተማመንን አዳብረህ ቅናትን ታስወግዳለህ፡፡



 የሳይኮሎጂ ምክሮች

  

እጅግ በጣም ስኬታማ የሆኑ ሰዎች 7 ልምዶች-(በነጋሽ አበበ)

ከአስራ አምስት ሚሊዮን ቅጂ በላይ ተሽጧል፤ በሰላሳ ቋንቋዎች ተተርጉሞም ለንባብ በቅቷል፤ በእኛው አማሪኛ ቋንቋም ተተርጉሞ መታተሙንም አውቃለሁ፡፡ ይህ መጽሐፍ “The 7 Habits of Highly Effective people” ይባላል:: “እጅግ በጣም ስኬታማ የሆኑ ሰዎች 7 ልምዶች” ብለን ቃል በቃል እንተርጉመው፡፡ የመጽሐፉ ደራሲ ስቴቨን ኮቬይ ይባላል፡፡ ይህ መጽሐፍ በግለሰብ ደረጃ ብልፅግናን (Personal development) ለመፍጠር እንዲረዱ ታስበው እስከ ዛሬ ድረስ ከተጻፉ መጽሐፍት መካከል ወደር የማይገኝለት ነው፡፡ ካላነበባችሁት እንድታነቡት እመክራለሁ፡፡ ያነበብነውም ደግመን ልናነበው ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡
የዚህ ድንቅ መጽሐፍ ደራሲ ስቴቨን ኮቬይ “ውስጣዊ ድል ከውጫዊ ድል ይበልጣል” ይላል፡፡ እዚህ ምድር ላይ ማግኘት የምንፈልጋቸውን ነገሮች በሙሉ ለማግኘት አስቀድመን ራሳችንን ማሸነፍ፤ የህይወታችን ሾፌር መሆን፤ ውስጣዊ ማንነታችንን መቆጣጠር ወዘተ አለብን ማለት ነው፡፡ “ከተማን ከሚመራ ሰው ይልቅ ራሱን የሚመራ ሰው ይበልጣል” ይላል ጠቢቡ ሰለሞን፡፡ ራስን ማሸነፍ ሌሎች ውጫዊ ነገሮችን የማሸነፊያ ቁልፍ ነው፡፡ በመቀጠል በቅደም ተከተል የምንመለከታቸው 7 ልምዶች ማንኛውም ሰው የግል ህይወቱ መሪ እንዲሆን በእጅጉ የሚያግዙ ናቸው፡፡ አሁን ቦታውን ለእነዚህ ልምዶች ለቀቅ እናድርግ እስኪ፡፡
1. ኃላፊነት ውሰዱ
ጅብ ከሄደ በኋላ የውሻ መጮህ ምንም ው.ጤት አያመጣም፤ ትርፉ ድካም ነው፡፡ ውጤት የሚያመጣው ጅቡ ከመምጣቱ በፊት አስቀድሞ በማነፍነፍ ድምጽ ማሰማት ነው፡፡ ሁኔታዎችን፣ ሌሎች ሰዎችን፣ ዓለምን ወዘተ የሚወቅሱ ሰዎች በህይወታቸው የረባ ቁም ነገር አያከናውኑም፤ ሁልጊዜም ኃላፊነትን የሚያሸክሙት ከእነሱ ውጪ ላለ ሌላ አካል ነው፡፡ ኃላፊነትን መሸከም ስንችል ነው የህይወታችንን ጉዞ አቅጣጫ መወሰን የምንችለው፡፡ የተሸከርካሪውን መሪ ለሌላ አካል አሳልፈን ሰጥተን የምፈልገው ቦታ አይደለም የደረስኩት፤ በፈለኩት ፍጥነት አይደለም እየተጓዝኩ ያለሁት ወዘተ ልንል አንችልም፤ ብንልም ዋጋ የለውም፡፡ የጉዞውን አቅጣጫ፣ ፍጥነት እና አድራሻ የሚወስነው አሽከርካሪው ነው፡፡ ልምዳችን መውቀስ፣ ጣት መጠቆም፣ ራስን መከላከል ወዘተ ከሆነ እውነቱን ለመናገር የሚወቀስ ነገር ማግኘት አይከብድም፡፡ ዘወትር የእናቴ መቀነት አደናቅፎኝ ነው ማለት ህይወታችን ባለህበት እርገጥ እንዲሆን በር ወለል አድርጎ ይከፍታል፡፡ ስለዚህ ለውጥ ለማምጣት፣ የራሳችን ሰዎች ለመሆን፣ ውስጣችንን ድል ለማድረግ ወዘተ ሁልጊዜም ለገዛ ራሳችን ህይወት ሙሉ ኃላፊነት እንውሰድ፡፡ ቃላችንን የምናከብር፤ በአልንበት ቦታ የምንገኝ፤ በገዛ ራሳችን ጥረት የምንፈልገውን ማንኛውንም ዓይነት ነገር እጃችን ለማስገባት መጓዝ ያለብንን ያህል ርቀት መጓዝ የምንችል ሰዎች እንሁን፡፡ “ስራ እኮ ጠፋ! እኔ ምን ላድርግ?!” ከማለታችን በፊት ስራ ለማግኘት የምንችለውን ድንጋይ በሙሉ መፈንቀላችንን እርግጠኛ እንሁን፤ ቀጣሪዎች የሚፈልጉትን ዕውቀት እና ክህሎት ይዘን ለመገኘት ጥረት እናድርግ፤ የተለመደውንም ያልተለመደውንም አማራጭ እንፈትሽ፡፡ ሳይኮሎጂስቶች “Life is 10 % what happens to us and 90 % how we react to it” ይላሉ፡፡ የህይወታችንን አብዛኛውን (90 %) ክፍል በምንፈልገው መልኩ መስራት እንችላለን ማለት ነው፡፡ የምናጭደው የዘራነውን ነው፡፡
2. የምትፈልጉትን ነገር አስቀድማችሁ እወቁ
ስቴቨን ኮቬይ “ነገሮች ሁለት ጊዜ ይፈጠራሉ” ይላል፡፡ የመጀመሪያው ፈጠራ የሚጠናቀቀው አእምሮአችን ውስጥ ነው፡፡ ከቤት ከመውጣታችን በፊት የምንሄድበትን ማወቅ ይኖርብናል፡፡ ከአንድ እና ሁለት፣ አምስት እና አስር ዓመት ወዘተ በኋላ ምንድን ነው ማግኘት፣ ማድረግ፣ መሆን ወዘተ የምንፈልገው? ለእነዚህ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ መስጠት ነገሮቹ በተጨባጭም ወደ ህይወታችን የሚመጡበትን ዕድል ከፍ ያደርጋል፡፡ “We rise to the level of our expectations” ይባላል፡፡ የምናገኘው የምናስበውን ነው፤ የምንደርሰው እንደርሳለን ብለን የምናስበው ከፍታ ድረስ ነው፡፡ ግባችንን ማወቃችን ትኩረታችንን ለመሰብሰብ ይረዳናል፤ ከነፈሰው ጋር አንነፍስም፤ በፈተና መካከል ጸንተን እንቆማለን፡፡ ሳይኮሎጂስቶች የህይወታችንን ግብ በቅጡ ለመለየት የሚረዳን አንዱ ሁነኛ መንገድ “የቀብራችን ዕለት እንዲነበብ የምንፈልገውን የህይወት ታሪካችንን መወሰን ነው” ይላሉ፡፡ ቁጭ ብለን ልናስብበት ይገባል፡፡
3. ቅድሚያ ለሚገባቸው ነገሮች ቅድሚያ ስጡ
“ሁሉ አማረሽን ገበያ አታውጧት” ይባላል፡፡ ቅድሚያ መስጠት ላለብን ነገሮች ቅድሚያ መስጠት አለብን፡፡ ሁለት እግር አለኝ ተብሎ ሁለት ዛፍ ላይ አይወጣም፡፡ ኮቬይ እንዲህ ይላል፡- “ራሳችሁን ከእነዚህ ሶስት አጉል ልምዶች በአንዱ መውቀስ ቢኖርባችሁ በየትኛው ነው የምትወቅሱት? (1) መስራት ያለብኝን ነገር በቅደም ተከተል መለየት አልችልም፤ (2) በአስቀመጥኩት ቅደም ተከተል መሰረት መስራት አልችልም፤ (3) በወሰንኩት ቅደም ተከተል መሰረት ለመስራት አስፈላጊው ቁርጠኝነት የለኝም፡፡ ብዙ ሰዎች ቁርጠኝነቱ የለኝም ነው የሚሉት፡፡ ጠለቅ ብለን ከመረመርነው ግን እውነቱ ሌላ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ እውነቱ ቅደም ተከተሉ ውስጣችን በጥልቀት አለመስረጹ ነው፡፡ ልምድ 2ን ማለትም የህይወት ግባችንን አስቀድመን በሚገባ ለይተን በሚገባ ውስጣችንን መቅረጽ አለመቻላችን ነው”::
4. በጋራ እኩል ተጠቃሚነት መርህ ተመሩ
ከተቃራኒ ፆታ ጀምሮ እስከ የንግድ ስራ ግንኙነት ድረስ በጋራ እኩል ተጠቃሚነት መርህ መመራት ትልቅ ጥቅም አለው፡፡ “አዎ! በሚገባ አምንበታለሁ፡፡ በእኩል ተጠቃሚነት መርህ ነው ህይወቴን የምመራው፡፡” ትሉ ይሆናል፡፡ እንደምትሉት እንደምትኖሩ ግን እርግጠኛ ሁኑ፡፡ ለማሸነፍ ከመጣር ይልቅ እንዴት በጋራ እኩል ተጠቃሚ ለመሆን ጥረት አድርጉ፡፡ የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን፣ ከሌላው ከፍ ብሎ ለመታየት፣ ልክ ሆኖ ለመገኘት ወዘተ ከመጨነቅ ይልቅ በጋራ እኩል እንዴት ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻል ማሰብ እና ይህንን መርህ በየትኛውም የግንኙነታችን መረብ ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ ይበልጥ ውጤታማ ያደርገናል፡፡
5. መጀመሪያ ለመረዳት ጥረት አድርጉ
መጀመሪያ ስንረዳ የሚረዱንን እናገኛለን፡፡ ብዙ ጊዜ ግን በአንጻሩ ጊዜያችንን የምናጠፋው ሰዎች እንዲረዱን በመፍጨርጨር ነው፡፡ ቆም ብለን  “ምንድነው እስኪ እያሉ ያሉት? ልክ ይሆኑ ይሆን? በየትኛው ማዕዘን ነው እነሱ ጉዳዩን ያዩት?” ወዘተ ብሎ በቀናነት ማሰብ እና ሰዎችን ለመረዳት ጥረት ማድረግ ጥሩ ነው፡፡ ሰዎችን የመረዳት ችሎታችን ጥሩ ሲሆን የሚረዱንን ሰዎች ቁጥርም ይጨምራል፡፡
6. 1 + 1 = 3
“ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” ትልቅ መልዕክት ያለው አባባል ነው፡፡ በጋራ የሚሰሩ ስራዎች በግል ከሚሰሩ ስራዎች ይልቅ የላቀ ውጤት ያመጣሉ፡፡ አንድ እጅ ብቻውን አያጨበጭብም፡፡ ሩጫን በመሰለ የግል ጥረትን በከፍተኛ ሁኔታ በሚጠይቅ የውድድር ዘርፍ እንኳን አትሌቶቻችን ሲተባበሩ የሚያስመዘግቡትን አንጸባራቂ ድል እናውቀዋለን፡፡ በየትኛውም አጋጣሚ በጋራ የመስራትን መንፈስ ማዳበር ጠንካራ ያደርጋል፤ የበዛ ፍሬም ያፈራል፡፡ አብረን መብላት ብቻ ሳይሆን አብረን መስራትንም ባህላችን እናድርግ፡፡ ስቴቨን ኮቬይ እንደሚለው “አንድ ሲደመር አንድ ከሁለት በላይ ነው”፡፡

7. መጋዛችሁን ሳሉ
ስቴቨን ኮቬይ መጽሐፉ ውስጥ ግሩም አፈ ታሪክ አለ፡፡ አንድ ተጓዥ መንገደኛ በአንድ ጫካ ውስጥ አቋርጦ ሲያልፍ አንድ ምስኪን እንጨት ቆራጭ ላቡ ጠፍ እስከሚል ድረስ ያለምንም እረፍት እንጨት ሲቆርጥ ይመለከታል፡፡ ተጓዡ መንገደኛ ቆም ይልና የመጋዙን መደነዝ አስተውሎ ኑሮ “ወዳጄ! ለምን መጋዝህን ዕረፍት ወስድህ አትስለውም?” ይለዋል፡፡ ልፋ ያለው እንጨት ቆራጭ “አይ ለሱ እንኳን ጊዜ የለኝም” የሚል የዋህ ምላሽ ይሰጠዋል፡፡ ይኼ ምስኪን እንጨት ቆራጭ ዕረፍት ወስዶ መጋዙን ቢስል በተሻለ ቅልጥፍና ብዙ እንጨት መቁረጥ እንደሚችል አልተረዳም፡፡
የተራ ቁጥር ሰባት ልምድ መልዕክት ቀላል እና ግልጽ ነው፡፡ በቂ ዕረፍት ምንጊዜም አድርጉ ነው፡፡ ከስራ በኋላ ራሳችሁን ዘና የማድረግ ልምምዱ ይኑራችሁ፡፡ መዝናናት ለጊዜው ከሚሰጠው ደስታ ባሻገር ለቀጣይ ስራ ያዘጋጃል፡፡ ሁልጊዜም እንደምለው ትልልቅ ኩባንያዎች ወጪ ችለው፣ ወርሃዊ ደሞዝ መክፈላቸውን ሳያቋርጡ ሰራተኞቻቸውን የሚያዝናኑት በጣም ቸር ስለሆኑ አይደለም፡፡ ይልቁንም የተዝናና ሰራተኛ ይበልጥ ውጤታማ እንደሚሆን እና እነሱንም ይበልጥ ውጤታማ እንደሚያደርጋቸው ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ነው፡፡
አንድ አንድ ሰዎች “እኔ መዝናናት አይሆንልኝም” ይላሉ፡፡ “መዝናናት ራሱን የቻለ ችሎታ ነው” ይላል አንድ ሌላ ወዳጄም፡፡ በመሆኑም “እንዴት እንዝናና?” የሚል ጥያቄ ያላችሁ ሰዎች እነዚህን የመዝናኛ አማራጮች እንድትፈትlቸው እጋብዛለሁ፡- ዋና ዋኙ፤ ከወዳጅ ዘመዶቻችሁ ጋር አስደሳች ጊዜ አሳልፉ፤ ዮጋ ስሩ፤ ዳንስ ደንሱ፤ ከከተማ ከተቻለም ከሀገርም ወጣ ብላችሁ ጎብኙ፤ ደስታ ይሰጠኛል ብላችሁ የምታስቡትን የትርፍ ጊዜ የመዝናኛ አማራጭን (Hobby) ሞክሩ፡፡






ከሰዎች ጋር ያለንን ተግባቦት ለማዳበር የሚረዱ ጠባያት-(በዘመነ ቴዎድሮስ)

1. ጥሩ አድማጭ መሆን
ተግባቦትን ለማዳበር ከሚረዱ ጠባያት ዋነኛው ጥሩ አድማጭነት ነው፡፡ ሰዎች በሚናገሩበት ሰዓት ተናግረው እስኪጨርሱ አለማቋረጥ፤ ዓይናቸውን መመልከት፤ በንግግር መሃልም መረዳታችሁን ለማመልከት ጭንቅላታችሁን ወደ ላይና ወደ ታች መነቅነቅ፤ ተናግረውም ከጨረሱ በኋላ መናገር የፈለጉትን ሃሳብ በጥቂት ቃላት ማጠቃለል የጥሩ አድማጭነት ምልክቶች ናቸው፡፡
2. የፊት ገጽታችንና የእጅ እንቅስቃሴአችን
በንግግር ወቅት ያለን የፊት እና የእጅ እንቅስቃሴ ስለምንናገረው ሃሳብ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ አለ፡፡ ለምሳሌ አስደሳች ሃሳብ ለመናገር እየሞከርን የፊት ገጽታችንን ማኮሳተር፤ ማጨማደድ እና የዓይን ሽፋሽፍትን መሰብሰብ ለአድማጭችን ተቃራኒ መልዕክት ይልካል፡፡ ስለዚህም ከምንናገረው ሃሳብ ጋር ውህደት ያለው የፊት ገጽታና የእጅ እንቅስቃሴ ሊኖረን ይገባል፡፡
3. ፍሬ ሃሳቡን በተወሰኑ ቃላት መግለጽ
የሰው ልጅ ትኩረትን ሰጥቶ አንድን ድርጊት መከወን የሚችው ለጥቂት ደቂቃዎች ስለሆነ በንግግር ወቅት በጥቂት ቃላት የምንፈልገውን ሃሳብ መግለጽ ይገባል፡፡ የምናናግረውም ሰው በዚያች በሚያናግረን ሰዓት ብዙ የሚያሳስቡት እና ጊዜ ሊሰዋላቸው የሚፈልጋቸው ብዙ ጉዳዮች እንዳሉት በማመን አጭርና በተመረጡ ቃላት የተሟላ ንግግር ብናደርግ ጥሩ ተግባቦት ይኖረናል፡፡
4. ትኩረት የሚያሳጡ ነገሮችን ማራቅ
ተንቀሳቃሽ ስልክ እንዲህ የዕለት ተዕለት ኑሯችን ውስጥ ዘልቆ በገባበት ጊዜ ውስጥ ከሰዎች ጋር በምንነጋገርበት ወቅት የምንጠቀማቸው ከሆነ ተገቢ ያልሆነ ትርጉም ይሰጣል፡፡ ለምናናግረው ሰው ውይም ስሚናገረው ሃሳብ ግድ እንደሌለን ያሳብቃል፡፡ ስለዚህም በንግግር ወቅት ተንቀሳቃሽ ስልካችንን ጨምሮ የምንከውነውን ማንኛውንም ስራ አቁመን ሙሉ ትኩረታችንን በመስጠት ልናዳምጥ እንዲሁም ምላሽ ልንሰጥ ይገባል፡፡
5. አቀማመጥን ማስተካከል
ወደ ጀርባችን ተለጥጦ መቀመጥ፤ ጀርባችንን መስጠት ወይም ፊትን ወደ ተቃራኒው አቅጣጫ ማዞርን የመሳሰሉ አቀማመጦች ተግባቦትን አስቸጋሪ ሊያደርጉ ስለሚችሉ ወደ ምናናግረው ሰው አቅጣጫንን ማስተካከል እንዲሁም ጠጋ በማለት አቀማመጣችንን ማስተካከል ይገባናል፡፡
6. የሚያናግሩትን ሰው ስሜት መረዳት
እጅግ የሚያሳዝን ታሪክ እየተነገረን ስሜታቸውን ከቁብ ሳንቆጥር ቅጭም ባለ አኳኋን “የምተለው ይገባኛል” ብንል ተአማኒነት ያሳጣል፡፡ የተናጋሪውን ስሜት ወደእኛም ዘልቆ እንዲገባ መፍቀድ ከቻልን መልካም ተግባቦት ይኖረናል፡፡
7. ንግግርህ ፍሰት ያለው እና ያልተዘበራረቀ እንዲሆን ማድረግ
ከአንድ ሃሳብ ወደ ሌላ ሃሳብ መዝለል ውልና ማሰሪያ የሌለው ንግግር፤ ውይይትና ክርክር ማድረግ መጨረሻቸው የማያምር ነው፡፡ ስለዚህም ትኩረትን በአንድ ሃሳብ ላይ ብቻ በማድረግ ያልተዘበራረቀ እንዲሁም ፍሰቱን የጠበቀ ንግግር ማድረግ እርሱንም አጠናቆ ወደሌላው መሻገር ተገቢ ነው፡፡
8. በየንግግሩ መሃል የሚገቡ ድምጾችንና የቃላት ድግግሞሽን ማስቀረት
ብዙውን ጊዜ ሰዎች ሃሳባቸውን ከመከታተል ይልቅ ወደዚህ ጽምጸት አትኩረው እንዲያፌዙ ይጋብዛል፡፡ ስለዚህም “አ….. “ “አም….” የሚሉ ድምጸቶችን ማስወገድ ይገባል፡፡ እንዲሁም “እና” ፤ “ማለት ነው” እና “ምናምን” የሚሉ ቃላትን መደጋገም ንግግራችንን አሰልቺ ሊያደርጉት ስለሚችሉ ማስወገድ ይገባል፡፡
9. የድምጻችንን ቃና እንደየሃሳባችን ማቀያየር
በንግግር ወቅት አንድ ቃና ብቻ ያለው ወጥ ንግግር ማድረግ፤ ለሃዘኑም ለደስታውም ለቁጣውም ተመሳሳይ ድምጸት መጠቀም የአድማጭ ትኩረት እንዲበታተን የሚጋብዝ ነውና አንዴ ከፍ አንዴ ዝቅ አንዳንዴም ለጥቂት ሰኮንዶች ዝም እያልን በተለያየ ቃና የታጀበ ንግግር ማድረግ የአድማጭን ትኩረት ለመሳብና እስከ ንግግሩ መጨረሻ ሰብስቦ ለማቆየት ይረዳል፡፡


የበታችነት ስሜትን ማሸነፍ-(በከበደ በከሬ)

የበታችነት ስሜት ምንድነው?
የበታችነት ስሜት ማለት ስለራስ ማንነት፣ ብቃት፣ ችሎታ ወይም በሌሎች የህይወት ገጽታዎች ከሌሎች ሰዎች በታች እንደሆኑ ማሰብና ስሜቱንም መለማመድ ነው፡፡
ይህ ከሌሎች በታች እንደሆኑ ማሰብ በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሠረተ ሳይሆን በተለያዩ አሉታዊ ጫናዎች የተፈጠረ አስተሳሰብና ስሜት ነው፡፡ የበታችነት ስሜት ለራስ ዋጋ አለመስጠት፣ ስለራስ ብቃትና ችሎታ መጠራጠር እንዲሁም በማንኛውም መለኪያ ከሌሎች ሰዎች ጋር እኩል እንዳልሆኑ ተቀብሎ መኖር ነው፡፡
የበታችነት ስሜት በተጨባጭ ነባራዊ
 እውነታዎች ላይ መሠረት በማድረግ የሚሰጥ ምላሽ ሳይሆን ትክክለኛ ባልሆኑ በአብዛኛው መሠረተ-ቢስ በሆኑ ነጥቦች ላይ በመመርኮዝ ሰዎች ለራሳቸው የሚሰጡት የግምገማ ውጤት ነው፡፡
የበታችነት ስሜት ሰዎች ለራሳቸው የሚሰጡት ዋጋ በመሆኑ ውጫዊ ነገሮችን በመቀያየር የሚለወጥ ነገር አይደለም፡፡ ከሌሎች ሰዎች ጋር እኩል ለመሆን በስራ እጅግ ስኬታማ መሆን፣ ገንዘብ ሊገዛ የሚችለውን ነገር ሁሉ መግዛት፣ መዝናናት፣ …..የበታችነት ስሜትን አያጠፋም፡፡ መንስኤው የሰዎች አስተሳሰብ በመሆኑ፣ ራሳቸውን የሚያዩበት መስፈርት መለወጥ አለበት፡፡
ራሳችንን የምናይበት ሁኔታ በአካባቢያችን ያለውን ዓለም የምናይበትን መነጽር ይሰጠናል፡፡ ራሳችንን የምንመለከትበት መነጽር ትክክለኛ ካልሆነ፣ ዓለምንም የምናይበት መነጽር የተሳሳተ ነው፡፡
የበታችነት ስሜት ሌሎች ሰዎች በእኛ ላይ የሚጭኑት አስተሳሰብ ሳይሆን እኛው ራሳችን የምናሳድገው አስተሳሰብ ነው፡፡ ሰዎች ለአስተሳሰቡ መንስኤዎች ሊሆኑ ይችላሉ፤ ነገር ግን እኛ እሺ ብለን ካልተቀበልን በስተቀር ሌሎች ምንም ያህል ስለእኛ መጥፎ ነገር ቢናገሩ በእኛ ላይ ኃይል እንዳይኖረው ማድረግ እንችላለን፡፡ ከበታችነት ስሜት ለመውጣትም ከፍተኛው ድርሻ የእኛው ይሆናል፡፡
የበታችነት ስሜት ምልክቶች
የበታችነት ስሜት እንደ በሽታ ነው፡፡ አንድ በሽታ የራሱ የሆነ ምልክት እንዳለው ሁሉ፣ የበታችነት ስሜትም እንደ ስነ-ልቦና ችግር የራሱ ምልክቶች አሉት፡፡ በዚህ ክፍል የበታችነት ስሜት የሚሰማቸው ሰዎች በህይወታቸው የሚያሳዩትን ምልክቶችን አብረን እንመለከታለን፡፡
v  በህይወታቸው ውስጥ መልካም ነገር እንዳለ አያምኑም፡- እያንዳንዱ ሰው በህይወቱ ጠንካራና ደካማ ጎኖች አለው፡፡ የበታችነት ስሜት የሚሰማቸው ሰዎች በህይወታቸው ውስጥ ያለውን ደካማ/ የጎደለውን ነገር እንጂ ያላቸውን መልካምና ጠንካራ ነገር አያዩም፡፡ ሌላ ሰው ሲነግራቸው እንኳ እውነት እንደሆነ አምነው አይቀበሉም፡፡ ምክንያቱም እነርሱ ስለራሳቸው ከንቱ፣ ምስኪን፣ የሁሉ የበታች፣ ምንም ዋጋ የሌላቸው፣ …. አድርገው ደምደመዋል፡፡
v  ሰዎችን ለማስደሰት መኖር፡– የበታችነት ስሜት የሚያጠቃቸው ሰዎች ዋጋ እንዳላቸው ሌሎች ሰዎች እንዲያረጋግጡላቸው ይፈልጋሉ፡፡ ስለራሳቸው ጥሩ ነገሮችን በሚሰሙበት ጊዜ ደስ ይላቸዋል፡፡ ትንሽ ትችት ሲሰሙ ደግሞ እጅግ በጣም ይከፋቸዋል፡፡ ስለዚህ ሰዎች ስለእነርሱ ጥሩ ጥሩ ነገሮችን እንዲናገሩ ሌሎች ሰዎችን በማስደሰት ላይ ትኩረት ያደርጋሉ፡፡ የመልካም ግብረ-መልስ ረሃብተኞች ናቸው፡፡ የሰዎችን ፍላጎት ለማርካት ከሚጠበቅባቸው ዕርምጃ አልፈው ይሄዳሉ፡፡ ይህን የሚያደርጉት በጎ ነገር ማድረግ በራሱ ስለሚያስደስታቸው ሳይሆን ሰዎች ያንን አይተው እንዲያሞግሱአቸው ነው፡፡
v  በራስ የመተማመን መንፈስ ማጣት፡– በተጨባጭ እነዚህ ሰዎች ብቃት፣ ችሎታ፣ ልምድ ያላቸው ሊሆኑ  ይችላሉ፡፡ ከውጭ የሚያዩአቸው ሰዎች እንደ እነርሱ ችሎታ ቢኖራቸው ይመኙ ይሆናል፡፡ የበታችነት ስሜት የሚሰማቸው ሰዎች ግን ችሎታቸውንና ብቃታቸውን ለመግለጽ የሚያስችል በራስ የመተማመን መንፈስ የላቸውም፡፡ ከዚህም የተነሣ መስራት ከሚችሉት ኃላፊነት፣ መጠቀም ከሚችሉት መልካም ዕድሎች ይሸሻሉ፡፡ እንደ ችሎታቸው ለእነርሱ የሚገባውን መልካም ዕድል ሌሎች በራስ መተማመን ያላቸው ሰዎች ይጠቀማሉ፡፡
v  ከፉክክርና ውድድር መሸሽ፡– የበታችነት ስሜት የሚሰማቸው ሰዎች ውድቀትንና ትችትን በጣም ከመፍራታቸው የተነሣ ከሰዎች ጋር ከሚያወዳድራቸው ነገሮች ይሸሻሉ፡፡ በክንውን ከሌሎች ሰዎች ጥቂት አንሶ መገኘት ቀድሞውንም በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያለውን ስለራሳቸው ያላቸውን ግምት ክፉኛ ይጎዳል፡፡
v  ነገሮችን በወቅቱ አለመሥራት፡– አንዳንድ የበታችነት ስሜት የሚሰማቸው ሰዎች ተገቢውን ሥራ በተገቢው ጊዜ ለመስራት የተነሳሳ መንፈስ የላቸውም፡፡ ምክንያቱም ‹‹ምንም ብሠራ፣ ውጤቱ ያው የማይረባ ነው፤ እኔ ጥሩ ነገር መስራት አልችልም›› የሚል አስተሳሰብ ስላላቸው ነው፡፡ ስለዚህ አሁን መስራት የሚችሉትን ነገር ‹‹ነገ እሰራለሁ›› እያሉ ቀጠሮ ይሰጣሉ፡፡
አንዳንዶች ደግሞ የሚሰማቸውን የበታችነት ስሜት ለማካካስ ማለትም በሰዎች ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ብለው መስራት ከሚገባቸው በላይ ይሰራሉ፡፡ ከዚህም የተነሳ በሚሰሩት ስራ የተከናወነላቸው ስኬታማ ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ሆኖም በውስጣቸው ለራሳቸው የሚሰጡት ዋጋ በዚህ ስኬት አይለወጥም፡፡
v  ስህተት ፈላጊዎች ናቸው፡– እነዚህ ሰዎች በህይወታቸው ውስጥ ካለው አዎንታዊ ነገር ይልቅ አሉታዊውን የማየት ልማድ አላቸው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በሌሎች ሰዎች ህይወት ውስጥም ጥሩ ነገር ከማየት ይልቅ መጥፎ ነገሮችን ማየት ይቀናቸዋል፡፡ ለሰዎች የማይታያቸው ስህተት ለእነርሱ ይገለጣል፤ ነገር ግን ግልጽ የሆኑትን መልካም ነገሮች ለማየት አይቀናቸውም፡፡
የበታችነት ስሜት መንስኤዎች
ለበታችነት ስሜት ዕድገት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል ዋና ዋና የሆኑትን ጥቂት ነጥቦችን እንመለከታለን፡፡
«  ክፉ የአስተዳደግ ሁኔታ፡– ወላጆች ልጆቻቸውን ለማሳደግ የሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች አዎንታዊ ካልሆኑ ልጆች ስለራሳቸው ያላቸው አስተሳሰብ አሉታዊ ይሆናል፡፡ ልጆች ስህተት ሲፈጽሙ፣ ሙከራ አድርገው ሳይሳካላቸው ሲቀር፣ አንድን ነገር ለመስራት ጥረት ሲያደርጉ …. ወላጆች የሚሰጡት አስተያየት አሉታዊ ሲሆን ልጆች የሆነ ችግር እንዳለባቸው ያስባሉ፡፡ ለምሳሌ ወላጆች የሚሰጡት ምላሽ ‹‹አንተ ደደብ ነህ፣ ይህን መስራት ያቅትሃልን! አንተ አትችልም፤ እንደ ሌሎች ልጆች ጎበዝ አይደለህም›› በሚሉበት ጊዜ ልጆች እንደተባሉት እንደሆኑ ያስባሉ፣ በዚያውም አስተሳሰብ ያድጋሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ከወላጆቻቸው የሰሙአቸውን ነገሮች በድጋሚ ከመምህራንና ከሌሎች ሰዎችም ይሰማሉ፡፡ ይህ ሲሆን አባባሎቹ እነርሱን እንደሚገልጹ አድርገው ይቀበላሉ፡፡ የልጅነት ጊዜ ቢያልፍም፣ በልጅነት ስለራሳቸው የሰሙአቸው መጥፎ ነገሮች ከእነርሱ ጋር ዕድሜ ልክ ይቆያሉ፡፡
ለውስንነቶች የሚሰጡ አሉታዊ ምላሾች፡– ሰብዓዊ ፍጡር ውስን ነው፡፡ እያንዳንዱ ሰው የራሱ ውስንነት አለው፡፡ አንዳንዱ ውስንነት ከችሎታ፣ ከአካል፣ ከማኅበራዊ ኑሮ፣ ከኢኮኖሚ፣ ….. ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚህ ውስንነቶች አንዱ ሰው ከሌሎች የተለየ እንዲሆን ያደርጋሉ፡፡ ሰዎች እነዚህን ውስንነቶች/ልዩነቶችን እንደ ጉዳት ካሰቡ የበታችነት ስሜት ይሰማቸዋል፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው ቁመቱ አጭር ቢሆን፣ አጭር መሆኑ ከሌሎች ሰዎች ልዩ እንዲሆን አደረገው ማለት ነው፡፡ አጭር መሆኑን የሚመለከትበት ሁኔታ ራሱን እንዲቀበል ወይም እንዳይቀበል ሊያደርገው ይችላል፡፡
«  የስነ–ልቦና ጥቃት ሰለባ መሆን፡– ሰዎች በህይወታቸው ውስጥ የስነ-ልቦና ጥቃት የተፈጸመባቸው ከሆነ፣ ከጥቃቱ የተነሳ ራሳቸውን ሊጠሉ ይችላሉ፡፡ ይህ ጥቃት በወላጅ፣ በጓደኛ፣ በስራ ባልደረባ ወይም በሌሎች ሰዎች ሊፈጸም ይችላል፡፡
«  በተደጋጋሚ ችላ መባል፡– በልጅነትና በወጣትነት እንዲሁም በጎልማሳነት ወቅትም በሰዎች ዘንድ በተከታታይነት ችላ መባል ወደ በታችነት ስሜት ሊያመራ ይችላል፡፡ በተለይ በወላጅ፣ በጓደኞች እንዲሁም በአሰሪዎች ዘንድ ሆን ተብሎ ችላ መባል ግለ-ምስልን ይጎዳል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ዕውቅና/አድናቆት ሲገባቸው ያለማግኘትና እንዲህ ዓይነት ሁኔታ መደጋገሙ ‹‹ለእኔ ዓይነቱ ስለማይገባ ነው›› የሚል አስተሳሰብ እንዲሳያድጉ ምክንያት ይሆናል፡፡
«  ያለመሳካት መደጋገም፡– ለአንዳንዶች ውድቀት የስኬት መማሪያ መድረክ ሲሆን ለብዙዎች ግን ወደፊት ሌሎች መልካም ዕድሎችን እንዳይሞክሩ በር የሚዘጋ ክስተት ይሆናል፡፡ በተደጋጋሚ ሞክሮ ስኬት ማጣት፣ ሰዎች ለራሳቸው ያላቸውንም ግምት ይጎዳል፡፡ ‹‹ለእኔ ያልተሳካልኝ፣ የሆነ ችግር ቢኖረኝ ነው›› ብለው ማሰብ ይጀምራሉ፡፡ በተለይ ልጆች በትምህርት ቤት ውስጥ ዝቅተኛ ውጤት ሲያመጡ፣ ገንቢ በሆነ መንገድ የሚረዳቸው ሰው ካልተገኘ በስተቀር፣ ከሌሎች ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ውጤት ማግኘታቸው ራሳቸውን ከሌሎች አሳንሰው እንዲያዩ ያደርጋቸዋል፡፡ በትምህርት ካልተሳካላቸው፣ በሌሎችም የህይወት መስኮች እንደማይሳካላቸው ያስባሉ፡፡




ጥረትዎን ስኬታማ ለማድረግ የሚያግዙ 5 ምክሮች-by Teshome Tadesse



1. ራስን በአንድ ነገር ሳይገድቡ ሌሎች አማራጮችን መፈለግ
አንድ የሙዚቃ ሙያ፣ ትወና፣ ድርሰት፣ አነቃቂ ንግግሮች እና የህክምና ሙያ ባለቤት የሆነ ሰው፤ የተለያዩ የሙያ ስብጥሮች ባለቤት መሆኑ ጥረቱ ፍሬ ማፍራቱን እንዳመላከተውና በዚያው እንዲቀጥል እንዳገዘው ተናግሯል።
የባለ ብዙ ሙያ ባለቤት መሆኔ በተለይም በህይወቴ ውስጥ የተለያዩ ነገሮችን እንዳውቅ እና ስኬታማ እንድሆን አድርጎኛል ነው ያለው።በመሆኑም ሰዎች ልባቸው የሚጠቁማቸውን ፍላጎት ለማሳካት እና ጥረታቸውን ከዳር ለማድረስ በአንድ ነገር ብቻ መወሰን እንደሌለባቸው መክሯል።
2. ስራዎችን መልካም ሁኔታ ላይ በምንሆንበት ጊዜ መጀመር
ሰዎች ጥረታቸው ስኬታማ እንዲሆን የሚሰሩትን ስራ መጥፎ ሁኔታ ባጋጠማቸው ጊዜ መጀመር እንደሌለባቸው ይመከራል።በዚህም ሰዎች በመልካም ስሜት ነገሮችን ማከናዎን ከቻሉ ጥረታቸው ፍሬ ያፈራል ነው የተባለው።ከዚህም በተጨማሪ ሰዎች ስኬት ማስመዘገብ ሲጀምሩ በውጤታማነታቸው ረክተው ጥረታቸውን ማቋረጥ አይገባቸውም፤ የመጀመሪያው ስኬት ኀለሌላ ድል መሰረት ነውና።

3. ልጅ በነበሩበት ጊዜ ምን መሆን ነበር የሚፈልጉት? አሁንስ ምን የተለወጠ ነገር አለ?
 የሚለውን ጥያቄ ከግምት ማስገባትብዙ ጊዜ ሰዎች በህፃንነት ዘመናቸው መሆን የሚፈልጉት የራሳቸው ምኞት ይኖራቸዋል።ሃኪም፣ መምህር፣ ጋዜጠኛ፣ የስነ ልቦና ባለሙያ፣ ደራሲ አልያም የሌሎች ሙያዎች ባለቤት የመሆን ፍላጎት በሁሉም ዘንድ ይታያል።በዚህም በልጅነታቸው የተመኙትን ሙያ አግኝተው በዘርፉ ስኬታማ ለመሆን ጥረት አድርገው የተሳካላቸው ብዙ ሰዎች ይኖራሉ። አንዳንዶቹም ስኬት ሊርቃቸው ይችላል።በህፃንነታቸው የፈለጉትን ሙያ ትተው በሌላ ሙያ የተ
ሰማሩ ሰዎች በጊዜ ሂደት በተሰማሩበት ሙያ ፍላጎት ሊያጡ ይችላሉ።ይህ ፍላጎት ማጣትም በውጤታማነታቸው ላይ ተፅዕኖ የማሳደር አቅሙ ከፍተኛ በመሆኑ፤ በተሰማሩበት መያ ስኬታማ የሆኑ ሰዎችን አርዓያ ማድረግ ተገቢ ነው።

4. ለጥረታችን የአስተውሎት ካርታ ማዘጋጀት
ሰዎች ይህን ማድረጋቸው ሊሰሩት ስላቀዱት ነገር ምቹ ሁኔታ በመፍጠር እርግጠኛ ያልሆኑባቸውን ነገሮች ግልፅ ለማድረግ ያስችላቸዋል።ጥረታችንን ከመጀመራችን በፊት ስራየን የምሰራው ለራሴ ነው ወይስ ለሌሎች? የሚለውን ጥያቄ ግልፅ ማድረግ ግድ ይላል።በዚህም ስኬት ላይ የሚያደርሰንን ጥረት ለመጀመር፥ ሙሉ እቅዳችን እና ፍላጎታችንን በቅደም ተከተል ማስፈር ተገቢ ይሆናል።ይህን የእቅድ ካርታ መሰረት ያደረገ ስራችንን በመጀመርም ስኬቱን በየመካከሉ እየገመገሙ መቀጠል ወሳኝ መሆኑ ተጠቁሟል።

5. የገንዘብ ችግር ከሌለ ባለን ጊዜ ምን መስራት እንወዳለን የሚለው ላይ ማተኮር
ሰዎች በቂ ገንዘብ እና ጊዜ ኖሯቸው ደስተኛ ወይም ስኬታማ ለመሆን ለህይወታቸው ጠቃሚ የሆነውንና በጊዜያቸው መስራት የሚፈልጉትን ስራ መምረጥ ይገባቸዋል።አንዳንዶቹ በገንዘባቸው ያላቸውን ጊዜ ተጠቅመው የበጎ አድራጎት ስራ ሊሰሩበት ይችላሉ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ቤተሰባቸውን ሊያዝናኑበት ይፈልጋሉ፤ ሌሎች ደግሞ የጀመሩትን ስራ ከዳር ለማድረስ አስፍላጊ ነገሮችን ሊያሟልበት ይችላሉ።በመሆኑም ሰዎች በቂ ገንዘብ ካላቸው እና ጥረታቸው ፍሬ እንዲያፈራ ካቀዱ ገንዘቡን ፈሰስ የሚያደርጉበትን ፍላጎታቸውን ማወቅ ይኖርባቸዋል ነው የተባለው።
Info source:-psychologytoday
And Zepsychologist Ethiopia

PREPAREDBY RYAN YIDENEKAL
DEBRE BIRHAN, ETHIOPIA
2011.E.C
የሳይኮሎጂ ምክሮች - sychology Reviewed by nestamereja on 5:35 AM Rating: 5

1 comment:

All Rights Reserved by NESTA MEREJA © 2014 - 2015
Powered By Blogger, Share by Star Tuan

please fill the following

Name

Email *

Message *

Theme images by konradlew. Powered by Blogger.